Monday, August 8, 2016

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክፍል ሁለት

Read in PDF
ካለፈው የቀጠለ
1.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት መሠረት
1.1. ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ስለ መበቀልዋና በወንጌልም ላይ ስለ መመሥረቷ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከረጅም ዓመታት ቀደም ብሎ እምነተ ክርስትናን የተቀበለች ሐዋርያዊትና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን እንደ ሆነች፣ የክርስትናን እምነትም በምድረ ኢትዮጵያ እንዳስፋፋች ከላይ ለመግለጥ እንደ ተሞከረው በታሪክ የተረጋገጠ ሐቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ በእስትንፋሰ እግዚአብሔር የተጻፈ የማይለወጥና የማይሻር የአምላክ ቃል እንደ ሆነ ታምናለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን በእስትንፋሰ እግዚአብሔር የተጻፈ ነው ብላ ያመነችውን መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ወደ ግእዝ፣ ቀጥሎም ወደ አማርኛ ቋንቋዎች ተርጉማ ለክርስትና መስፋፋት ከፍተኛ ድርሻ አበርክታለች፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት በኢትዮጵያ ምድር በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን አገዛዝ ከአረማዊ እምነት ወደ ክርስትና ለመመለስ መቻሉና ተጽፈው ያሉትም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ነበረ ያሳያሉ፡፡ በ1ኛቆሮ. 15፥3 ‹‹እኔ ደግሞ የተቀበልኩትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ. . . ›› እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያቱ ከጌታ የተቀበሉትን ትምህርተ ሃይማኖት ለተከታዮቻቸው አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በቅብብሎሽም ብቸኛ የትምህርተ ሃይማኖት ምንጭ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስና ከእርሱም በተገቢው መንገድ ተቀናብሮ የተዘጋጀው ትምህርተ ሃይማኖት ወደ እኛ ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት የምትባለው ከላይ እንደ ተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስንና በቅብብሎሽ ከሐዋርያት ሲተላለፍ የመጣውን ትምህርተ ወንጌል ተቀብያለሁ፣ ለትምህርቱም ተገዥ ወይም ታዛዥ እሆናለሁ፣ ትምህርቱም የሃይማኖቴ ውሳኔ ነው ብላ በማመንዋ ነው፡፡
1.2. ቀደምት የሃይማኖት ድንጋጌዎች
በተለያየ ጊዜ የተደረጉት የሃይማኖት ድንጋጌዎች ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ መመሪያዎችን በማወቅ ከጥፋት እንድትድንና እንድትጠበቅ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘችውን ጽድቅ አጥብቃ እንድትይዝ ለማድረግ የተደነገጉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ቀደምት የሃይማኖት ድንጋጌዎች በመቀበልና በማስተማር ስትገለገልባችው ቈይታለች፡፡
ሀ/ አመክንዮ ዘሐዋርያት
ይህ ሐዋርያት ጽፈውታል የተባለው የሃይማኖት ድንጋጌ ሲሞን መሠርይ የሚባለውን መናፍቅ ለመቃወምና የእርሱ ትምህርት ኑፋቄ እንደ ሆነ እንዲታወቅ ሐዋርያት የጻፉት ነው ብለው ግምታቸውን የሚሰጡ ወገኖች አሉ፤ ሐዋርያቱ የጻፉበት ምክንያት ይህም ይሁን ሌላ ድንጋጌው በሐዋርያት ስም ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን የሃይማኖት አበውና በቅዳሴ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ ሃ.አ ምዕራፍ 6 እና መጽሐፈ ቅዳሴ ምዕራፍ 4 ተመልከቱ፡፡

Monday, June 6, 2016

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ይቅርታ……….
ውድ አንባቢዎቻችን ለረጅም ጊዜ ምንም የጹኁፍ ሥራ ባለማቅርብ መቆየታችን ይታወቃል። ስለ ተፈጠረዉ ሁኔታና መቛረጥ ይቅርታ በመጠየቅ በቀጣይነት በተከታታይ የተሃድሶን አተያይ የሚያንጸባርቁ በወንጌል አገልጋዮች የተዘጋጀዉን የለውጥ ጥሪና አመላካች ሥራ እንቀርብላቸዋለን። በዚህ መሠረት ይህ የመጀመሪያ ክፍል ይሆናል።
1.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአስተዋጽኦ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በመቀበልና በአገራችን በማስፋፋት የመጀመሪያዋ መንፈሳዊት ተቋም ናት፡፡ ይች ቤተ ክርስቲያን ክርስትና በተረጋገጠ ሁኔታ በኢትዮጵያ ምድር እንዲመሠረት አድርጋለች፡፡ ወደ አገራችን ወደ ኢትዮጵያ ቃለ ወንጌል የደረሰው በኢትዮጵያዊው ጀንዳረባ አማካኝነት እንደ ሆነ በግብረ ሐዋርያት ምዕራፍ 8፥26-40 ከተጠቀሰው ታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡ ጃንደረባው እምነተ አይሁድ ይከተል ስለ ነበር ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት በ34 ዓ.ም. ገደማ ክርስቶስን አምኖና ተጠምቆ ተመልሷልና የወንጌልን አገልግሎት እንደ ጀመረ ይታመናል፡፡

‹‹የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ወይም ኢትዮጵያና ክርስትና የተዋወቁት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ ነው፡፡ ይህም የሆነው ከጌታ ልደት በኋላ በ፴፬ ዓ.ም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ተጠምቆ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ዐዲሱን ሃይማኖቱን ለሀገሩ ሕዝብ አስተምሯል›› ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 20፡፡
በምሥራቅ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ተከትለው በወደብ ደረጃ የተመሠረቱና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው ብዙ ከተሞች ነበሩ፡፡ ከ64 ዓ.ም ጀምሮ ሮማውያን ክርስቲያኖችን ማሳደድ ጀመሩ፤ እስከ 313 ዓ.ም ድረስም ድርጊቱ ቀጥሏል፡፡ ይህ ዘመን ዘመነ ሰማዕታት በመባል ይታወቃል፡፡ በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች መጥተዋል፡፡ በንግድ ምክንያትም መምጣታቸው ይነገራል፡፡ በንግድ ምክንያት የመጡት ክርስቲያኖች ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል፡፡ ፍሬምናጦስም (አባ ሰላማ) በንግድ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ከተሞች ከመጡ ቤተሰቦች የተገኘ ነው፡፡

Saturday, February 6, 2016

አቤሜሌክና ማኅበረ ቅዱሳን

ክፍል 1
ከመምህር ይልቃል ቃሉ

        በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ታላላቅ ድንቅ ሥራዎች ከታዩበት የመጽሐፍ ክፍል ውስጥ መጽሐፈ መሳፍንት ተጠቃሽ ነው፡፡ መጽሐፈ መሳፍንት ከኢያሱ ሞት እስከ ንጉሣዊ አስተዳደር ጅማሬ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በተስፋይቱ ምድር የነበረውን ኑሮ ያመለክታል፡፡ በአንድ በኩል ዐመፀኝነት በመብዛቱ በሕዝቡ ላይ የደረሰውን የእግዚአብሔርን ቅጣት፤ በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር በመከራና በጭንቀት ጊዜ ለቀረበለት የእርዳታ ጩኸትና ልመና ምላሽ በመስጠት የተለያዩ መሪዎች (መሳፍንትን) አስነሥቶ የሕዝቡን ጠላት እንደመታና ሰላምን እዳሰፈነ ይተርካል፡፡ ከዚህም ሌላ መጽሐፉ አስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት ለአባቶቻቸው የተገባላቸውን የተስፋ ምድር እንደ ወረሱና እስራኤልም እንደ እግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ እንደ ተመሠረተች ይናገራል፡፡ ነገር ግን እስራኤል ከነዓን ከገባች በኋላ እግዚአብሔር ያደረገላትን ሁሉ ወዲያው ረሳች፤ ከከነዓናውያን ጣዖታትና እምነት ጋር ራሷን አጠላለፈች፡፡ 
የመጽሐፈ መሳፍንት መሠረታዊ ጉዳይ እግዚአብሔር የእስራኤል ጌታ መሆኑን መግለጽ ነው፡፡ እግዚአብሔርም በሉዓላዊ ሥልጣኑ ባዕዳን ወራሪዎችን ተጠቅሞ ሕዝቡ በጠፉ ጊዜ በመቅጣት በኪዳኑ የተጠቀሱትን ርግማን በመፈጸም (ዘሌ. 26፥14-45፤ ዘዳ. 26፥15-68) እንዲሁም ሕዝቡ ተጨንቆ ወደ እርሱ በሚጮኽበት ጊዜ ነጻ አውጪ መልእክተኞች በመላክ በእስራኤል ላይ ያለውን ንግሥና ይጠብቅ ነበር፡፡ የተመሠረተውም አዲስ መንግሥት እንዳይጠፋ ይከላከል ነበር፡፡ ምድሪቱም ከመልክዐ ምድራዊ አቀማመጧ የተነሣም በየጊዜው በተለያየ አቅጣጫ ከተሰነዘረባት የጣላት ወረራ ይታደጋት ነበር፡፡

        እግዚአብሔር አምላክ በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ ሕዝቡን በብርቱ ክንዱ ከጠላት አገዛዝ ከታደገባቸው መስፍኖች ውስጥ ጌዴዎን (ይሩበአል) ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ 
ጌዴዎን (ይሩበአል) እስራኤላውያንን በሦስት መቶ ሰው ከምድያማውያን እጅ በእግዚአብሔር ኃይል ከታደገ በኋላ እስራኤላውያን ያሉት ነገር ነበር ‹‹የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን፡- ከምድያም  እጅ አድነኸናልና አንተም ልጅህም የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን አሉት፡፡ ጌዴዎንም፡- እኔ አልገዛችሁም ልጄም አይገዛችሁም እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው›› መ.መሳ. 8፥22-23፡፡ የታደጋቸው ያዳናቸው ከጠላት ያስመለጣቸው እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ አንተ ንገስብን አሉት፡፡ የጌዴዎን መልስ ግን እጅግ ድንቅ ነበር፡፡ በመቀጠል እግዚአብሔር በጌዴዎን እድሜ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት እንድታርፍ አድርጓል፡፡ 
ለጌድዎን ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች የነበሩት ሲሆን ሴኬም ከምትባል ሥፍራ ከነበረችው እቁባት የወለደው አቤሜሌክ የሚባል ልጅ እንደነበረውና ጌዴዎንም በመልካም ሽምግልና እንደ ሞተ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢአስ መቃብር እንደተቀበረ መጽሐፉ ይተርካል፡፡ ይህን ሁሉ ስለ መጽሐፈ መሳፍንት ያነሳነው ከጌዴዎን በኋላ በእስራኤል የተፈጸመው ታሪክ ከዘመናችን ጋር ቁልጭ ብሎ እየታየ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ገዥ ንጉሥ መሆን ይፈልጋል፡፡ 

Wednesday, January 6, 2016

ኢየሱስ መዳናችንን ሊፈጽም ተወልዷል፡፡

ኢየሱስ ለሰው ልጆች ችግር ሁሉ የመፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ በሁሉ ነገር ላይ፣ ስለ ሁሉ ነገር የእርሱ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፡፡ ላልታደለው ዓለም፣ ለተቆረጠው ተስፋ፣ ኢየሱስ ብቸኛ የእርጋታ ምንጭ እና የተስፋ ፍጻሜ ነው፡፡
ከኢየሱስ በፊት የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉ ከንቱ የሆነበት ነበር፡፡
 ጽድቁ መርገም ጨርቅ፣
ዓላማው የማይሳካ፣
ተስፋው የማይፈጸም
ስራው በረከት የሌለው ነበር፡፡ 

የሰው ልጅ ሀሳቡን ተስፋ መቁረጥ ላይ አስደግፎ የሚንቀሳቀስበት ጊዜ፣ ሰይጣን እንደልቡ በሰው ላይ የሚጫወትበት ጊዜ፣ ጥበብ የጎደለበትና ጽድቅ የተረሳበት ጊዜ ነበር፡፡
“ከዚህ ቆስቋላ ሕይወት ማን ያድነኛል?” የሚለው ተማጽኖ የሰው ልጅ ሁሉ የማቋርጥ ድምጽ ሆኖ በመጠበቅና በመራብ የሚቃትትበት ጊዜ ነበር፡፡
ጌታ ሲወለድ ግን ታሪክ ተገልብጧል፡፡ የመርገም ጨርቅ የነበረው ጽድቅ በኢየሱስ ክርሰቶስ በኩል ፍጹም ሆኖ አብን ባረካበት መንገድ ተፈጽሟል፡፡ ኢየሱስ ጽድቃችን ኢየሱስ ቅድስናችን ኢየሱስ ልምላሜያችን ኢየሱስ የተስፋችን ፍጻሜ ኢየሱስ ሁሉመናችን ብለን እንጠራው ዘንድ ፍቅሩ ግድ ብሎን እግሩ ሥር ተንበርክከናል፡፡ 

Tuesday, November 10, 2015

ተሃድሶ የእምነት መግለጫዉን ይፋ አደረገ

ወደ እግዚአብሔር ቃልና ወደ ፈቃዱ ልንመለስና ሕይወታችንንና አገልግሎታችንን እንደ ቃሉ ልንቃኝና ልናርም ይገባል የሚል የለውጥ ጥያቄ በማንሣታቸውና ወንጌልን በማስተማራቸው ምክንያት የማያምኑትን እንደሚያምኑና ማንነታቸው ያልሆነውን መገለጫቸው እንደሆነ ተደርጎ ስማቸውን በማጥፋትና በመክሰስ ከእናት ቤተክርስቲያናቸው በግፍ የተገፉትና አሁንም በየሥፍራው በመከራ የሚገኙትን የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑትን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ማንነታቸውንና እምነታቸውን የሚገልጥ የእምነት መግለጫ ታትሞ በይፋ ተመረቀ፡፡ ጥቅምት 14/2008 ዓ.ም ከቀትር በኋላ እጅግ በደመቀ ሁኔታ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዐት ላይ ካህናት፣ ሰባክያን፣ ዘማርያንና ምእመናን የተገኙ ሲሆን በተጨማሪም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በጉባኤው ታድመዋል፡፡

የምረቃ ስነ ሥርዐቱ በካህናት አባቶች ጸሎት የተከፈተ ሲሆን በጉባኤው ላይ የቀረቡት ዋና ዋናዎቹ መርሐ ግብሮች መነባንብ፣ የእምነት መግለጫን ታሪካዊ አመጣጥና ይዘትን የሚያሳይ ትምህርት፣ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ በሚል ርእስ ስለተዘጋጀው የእምነት መግለጫ ይዘት ዳሰሳና እኛ የምናምነው እንዲህ ነው በማለት ይህን የእምነት መግለጫ ስላዘጋጁቱ የስነ መለኮት ምሁራንና ከልዩ ልዩ ሥፍራ የተውጣጡ ወገኖች ማንነታቸውን የሚገልጥ ሰነድና እምነታቸውን በጽሑፍ አዘጋጅተው ለማሳተም ያነሣሣቸውን ዓላማ የሚገልጥ ጽሑፍ ይገኙበታል፡፡

Friday, October 23, 2015

ማሕሌተ ጽጌ

Read in PDF
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመናት ቀመርና አቆጣጠር በየዓመቱ ከመስከረም 26- ኅዳር 6 ያለው ጊዜ ‹‹ወርሐ ጽጌ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹‹ጽጌ›› ማለት ‹‹አበባ›› ማለት ሲሆን በዚህ ወቅት የዱር ዕፀዋት የሚያብቡበት፣ ለዐይን ድንቅ የሆነ ኅብረ ቀለም ያለው የዱር ሳር ልምላሜና ጸደይ የምንመለከትባቸው ወራት ናቸውና በአበባው ጌታችንን ኢየሱስን፣ አበባው በተገኘባት  መሬት ድንግል ማርያምን እየመሰሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይልቁንም መሪጌቶች ያዜማሉ፤ ይቀኛሉ፤ ይዘምራሉ፤ ማሕሌተ ጽጌና ሰቆቃወ ድንግል የተባለውን ድርሰት እንዲሁም  በእነ ዘርዓያዕቆብ የተደረሰውን መልካ መልክ ሌሊቱን በሙሉ በመደጋገም ያዜሙታል፡፡
ነገር ግን ይህ ‹‹ማሕሌተ ጽጌ›› የተባለው አንስተኛ መጽሐፍ በሊቃውንት  ያልተመረመረና ያልታረመ ከመሆኑም ባሻገር በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ያለውን ልዩነት የማያውቁ እንዲሁም የማርያም ፍቅር አቃጠለን፤ አንገበገበን፤ ያሉ መሪጌቶች የደረሱት የክርስትና ሃይማኖት ካባና ጥምጣም የለበሰ እውነትን የሚቃረን ልብ ወለድ የሆነ አጉል ድርሰት ነው፡፡
ከብዙ ጥቂቶቹን በማንሳት ለምሳሌ ብንመለከት እንዲህ ይላል፡- ‹‹በከመይቤ መጽሐፍ ማዕከል ፈጣሪ ወፍጡራን፡፡ ለእረፍት ዘኮንኪ ጽላተ ኪዳን፡፡ ሰንበተ ሰንበታት ማርያም እለተ ብርሃን፡፡ ብኪ ይትፌስሁ ዘገነተ ጽጌ ጻድቃን፡፡ ወብኪ ይወጽኡ ኀጥእን እምደይን፡፡›› 
ትርጉም፡- ‹‹መጽሐፍ እንደሚል በፈጣሪና በፍጡራን መካከል መካከለኛ የሆንሽ የኪዳን ጽላት ማርያም  ሆይ ረፍቶች ሁሉ የላቅሽ ሰንበት ነሽ፡፡››
 ስለ እረፍት (ስለ ሰንበት)
ሰንበት ማለት ‹‹እረፍት›› ማለት ሲሆን፣ እግዚአብሔር  አምላካችን  ስድስት ቀናት የመፍጠር ሥራውን ከሠራ በኋላ አረፈ ዘፍ 2፥10 ይህን እለት ለሰዎች እረፍት እንዲሆናቸው ሰጣቸው፡፡ ዘዳ. 22፥10 ለአራት መቶ ሠላሳ ዘመን በስደትና በጦርነት ይማቅቁ ለነበሩ እሥራኤላውያን ይህ እረፍት (ሰንበት) ታላቅ ትርጉም ነበረው፡፡ በዐዲስ ኪዳን ለምንኖርና በክርስቶስ የማዳን ሥራ ለተዋጀን አማኞች ሁሉ ለዘመናት  የከበደንን የኀጢአት ሸክም የጣልንበት እውነተኛ እረፍታችን (ሰንበታችን) ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ማቴ.11፥28፡፡

Thursday, October 22, 2015

የኦርቶዶክስ ገቢ በቢሊዮን ቢቆጠርም የምዕመናኑ ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸምንጭ፡-http://www.ethiopianreporter.com/
-‹‹ምዕመናንን የመጠበቅ ተልዕኮ እየተወጣን አይደለም›› አቡነ ማትያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባዔ መደራጀት ስትጀምር ገቢዋ በመቶ ሺሕ ብር የነበረ ቢሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቢሊዮኖች ብር ማደጉን የገለጹት ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ፣ የምዕመናኗ ቁጥር ግን እየቀነሰ መሆኑን አስታወቁ፡፡ 

ፓትርያርኩ 34ኛውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔን አስመልክቶ ጥቅምት 8 ቀን 2008 .. እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያኗ ገቢ በቂ ነው ባይባልም፣ በየጊዜው እያደገ መጥቶ ከመቶ ሺዎች ብር ወደ ቢሊዮኖች ብር አድጓል፡፡ ይኼ የሆነውም ቤተ ክርስቲያኗ ከልጆቿ (ምዕመናን) ከምታገኘው ገቢ ባለፈ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፏ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የምዕመናን ዕድገት የኋልዮሽ እየሄደ መሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ዕድገቱ የኋልዮሽ መሆኑን የሚያውቅ ይኖር ይሆን? ችግሩንስ በሚገባ ተገንዝቦና በቁጭት ተነሳስቶ ችግሩን ለመቀልበስ የተደረገ ሙከራ አለ?›› የሚሉ ጥያቄዎቹን በማንሳት፣ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2008 .. የሚቆየው የሲኖዶስ ጉባዔ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ 
የኦርቶዶክሳውያን ተልዕኮ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መሆኑን ሁሉም የዕምነቱ ተከታዮች፣ በተለይ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አባቶች እንደሚያውቁ የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ከህሊና መቆርቆር እስከ ሕልፈተ ሕይወት የሚዘልቅ የመስዋዕትነት ዋጋ የሚጠይቅም መሆኑን መዘንጋት እንደሌለባቸው ለጉባዔው ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ 
ባህር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ፣ እስከ ምድር ጽንፍ ተጉዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረጉ ይቅርና በአገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምዕመናንን ማባዛት ብዙ እንዳልተሄደበት ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ትናንትና ስመ ክርስትና ሰጥታ በአባልነት የተቀበለቻቸው ልጆቿ፣ ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እየካዱ ወደ ሌላ ጎራ መቀላቀላቸው እየናረ መምጣቱን አክለዋል፡፡